ለአይነ ስውራን የቀረበ ዘመናዊ መሪ ወይም ኬን
ተመራማሪዎች የእይታ ችግር ያለባቸውን ሰዎች በእንቅስቃሴ የሚያግዝ ዘመናዊ ዘንግ ወይም ኬን ሰርተው አቀረቡ፡፡ በተለምዶ ነጩ ምርኩዝ በመባል የሚታወቀው ይህ አይነስውራን ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚጠቀሙበት ዘንግ ተጠቃሚዎቹ የሚኖራቸውን እንቅስቃሴ የተሸለ ቀላል እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ መደበኛው ዘንግ ከመሬት ጋር ሲጋጭ የሚኖረውን ድምጽ በመከተል አንድ አይነስውር በቀላሉ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ይችላል፡፡
ሳንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ይህንን መደበኛ ዘንግ እጅግ በማሻሻል አይነ ስውራን ከደህንነት ስጋት ነጻ ሆነው እንደፈለጉ እንዲንቀሳቀሱ በሚያስችል መልክ የሮቦት ቴክኖሎጂ አክሎበት ማቅረቡ ተነግሯል፡፡ ከራስ ነድ መኪኖች ቴክኖሎጂ ጋር ተጣምሮ የተሰራው ይህ ዘንግ በ400 ዶላር የቀረበ ሲሆን ተጠቃሚዎች እንደሚኖሩበትና እንደሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ምቹ የሆነ ድጋፍን የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡
ስማርት ዘንጉ በመንገድ ላይ ወይም በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ እንቅፋቶችን በመለየት በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ ለመንቀሳቀስ ምቹ የሆኑ ቦታወችን በመምረጥ መጓዝ የሚያስችል ነው፡፡ በዘርፉ ሌሎች ሴንሰር የተገጠመላቸው መሪ ዘንጎች ያሉ ቢሆንም ከአጠቃላይ ክብደታቸው እና ከሚያወጡት ዋጋ አንጻር ተፈላጊነታቸው አነስተኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከቴክኖሎጂ አንጻር እጥረት ያለባቸው በመሆኑ ማለትም ሴንሰሩ ከተጠቃሚው ፊት ለፊት ያለን ነገር ብቻ የሚያሳውቅ በመሆኑ ይህ ተሻሽሎ የቀረበው መሪ ዘንግ እጅግ ተመራጭ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
ከዚህ በፊት የነበረው ሴንሰር የተገጠመለት መሪ ዘንግ ወይም ኬን 50 ፓውንድ የሚመዝንና እስከ ስድስት ሺህ ዶላር የሚያወጣ ሲሆን የሄኛው ግን 3 ፓውንድ የሚመዝንና 400 ዶላር ብቻ የተቆረጠለት ነው፡፡ ተመራማሪዎቹ አሻሽለው ያቀረቡት መሪ ዘንግ በአለማችን ላሉ ከ250 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የእይታ ችግር ላለባቸው ሰዎች ጥቅም ይሰጣል ብለው ተስፋ አድርገዋል፡፡