አይፎን ለደንበኞቹ ያበሰረው መልካም ዜና ለስልክዎ መክፈቻ የፊት ገፅታዎን እንደመክፈቻ (Face ID) የሚጠቀሙ ከሆነ ከዚህ በኋላ የኮቪድ መከላከያ የፊት ጭንብልዎን (ማስክ) ማውለቅ ግድ አለማለቱ ነው፡፡
እንደ ዘቨርጅ ዘገባ አፕል በiOS 15.4 የስልክ ሥርዓተ-ክወና (operating system) እድሳቱ እንደሚያካተው የሚጠበቀው አዲስ ገፅታ ተጠቃሚዎች የፊት ጭንብላቸውን ሳያወልቁ የፊት ገፅታቸውን ለመክፈቻነት መጠቀም የሚችሉበትን አማራጭ ማካተቱ ነው፡፡
አዲሱ ገፅታ በአማራጭነት እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡ በዚህም ተጠቃሚዎች እንደፍላጎታቸው በጭምብል ወይም ያለጭምብል መጠቀም እንዲችሉ ምርጫቸውን ማስተካከል ይችላሉ፡፡
አፕል በምርቶቹ ላይ የሚጠቀመው የፊት ገፅታን እንደ ቁልፍ የመጠቀም ሂደት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አንዱ ውጤት ነው፡፡ ይህ የአፕል ስልኮችና ተያያዥ መሣሪያዎችን የመክፈቻ ሥርዓት ፊትን በባለ ሦስት ጎንዮሽ (3D) የማየት አቅም አለው፡፡
ሥርዓቱ ሰላሳ ሺህ የሚደርሱ የማይታዩ የኢንፍራሬድ ነጥቦችን ወደፊትዎ በመላክ ተፈላጊውን ምስል ያስቀራል፡፡ በመቀጠልም የማሽን ለርኒንግ ስልተቀመሮችን በመጠቀም ከዚህ ቀደም ካስቀመጠው ምስል ጋር የማነጻጸር ስራ በመስራት ስልኩን ለመክፈት የሚሞክረውን ሰው ማንነት ያረጋግጣል፡፡