የፌስቡክ እና ኢንስታግራም እናት ኩባንያ የሆነው ሜታ የ414 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተላለፈበት። ቅጣቱ ሜታ ላይ የተጣለው ኩባንያው ፌስቡክና ኢንስታግራም ተጠቃሚ ደንበኞች መረጃ ለማስታወቂያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ሜታ መተግበሪያዎቹን ከሚጠቀሙ ደንበኞች ህግን በጣሰ መልክ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ ማስታቂያዎችን እንዲቀበሉ አስገድዷል ተብሏል፡፡ ኩባንያው ቅድመ ሁኔታውን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ ደንበኞች አገልግሎቱን እንዳይጠቀሙ አድርጓል ሲል የአውሮፓ ህብረት ጠቅላላ የመረጃ ጥበቃ ደንብ ተቆጣጣሪ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል፡፡
ቀደም ሲል ሜታ ኩባንያ የግለሰቦችን መረጃ ለመጠቀም ፈቃደኝነታቸውን ይጠይቅ የነበረ ሲሆን ባይስማሙም እንኳን መተግበሪያዎቹን ከመጠቀም አያግዳቸዉም ነበር፡፡ ነገር ግን በአዲሱ አሰራሩ ሜታ ደንበኞቹ መረጃቸዉን ለማስታወቂያ እንዲጠቀምበት ፍቃደኛ ካልሆኑ መተግበሪያዋቹን መጠቀም እንዳይችሉ አድርጓል ነው የተባለው፡፡
ይህ ውሳኔ ከህብረቱ የግል መረጃ ጥበቃ ህግ ጋር ይጣረሳል ሲል ጉዳዩን ወደ ክስ እንደወሰደ የኒዉ ዮርክ ታይምስ ዘገባ አመላክቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም ሜታ ኩባንያ ጥፋተኛ ሆኖ ስላገኘው የ414 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት መጣሉም ነው የተገለጸው፡፡
ውሳኔው የኩባንያው ከማስታወቂያ የሚሰበስበውን ገቢ 7 ከመቶ የሚሆነውን አደጋ ላይ እንደሚጥልበትም ተነግሯል፡፡
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከጸና ሜታ የደንበኞችን መረጃ ለማስታወቂያ የማይጠቀም አዲስ ስሪት መተግበሪያ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ስራ ላይ ማዋል ይጠበቅበታልም ነው የተባለው፡፡