የ3ዲ ሕትመት የቤት ግንባታ ሂደትን ወደ አዲስ ከፍታ እየወሰደው ስለመሆኑ ከአሜሪካዋ ሂዩስተን ከተማ የተሰማው ዜና ያመለክታል፡፡ከ12 ቶን በላይ የሚመዝነው ግዙፉ የ3ዲ ማተሚያ ማሽን በአሜሪካ ውስጥ የመጀመሪያ የተባለለትን የ3ዲ ሕትመት ውጤት ባለ ሁለት ፎቅ ቤት እየገነባ መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
ማሽኑ በሂዩስተን ከተማ 370 ሜትር ስኩዌር ስፋት ያለውን ባለ ሦስት መኝታ መኖሪያ ቤት ለመገንባት የኮንክሪት ንጣፎችን ያለማቋረጥ እያመረተ ያቀርባል፡፡
ሁለት ዓመት እንደሚፈጅ የተነገረለት የቤቱ የግንባታ ሂደት ሃና በተባለ የንድፍ ተቋም እና ፔሪ የ3ዲ ግምባታ ኩባንያ እንዲሁም ሲቪ የግምባታ ኢንጂነሪንግ ተቋም ትብብር ዕውን እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
የሃና የንድፍ ተቋም መስራች እና የቤቱ ንድፍ አውጪ የሆኑት አርክቴክት ሌስሊ ሎክ የቤቱ ግምባታ ሂደት በአጠቃላይ 330 ሰዓታት የሕትመት ስራ እንደሚወስድ ተናግረዋል።
የ3ዲ የቤት የግምባታ ስልት ወደፊት በተሻለ ፍጥነት እና በርካታ ቤቶችን በርካሽ ለመገንባት እንደሚረዳ የዘርፉ ባለሞያዎች ተስፋ ነው፡፡