አነጋጋሪው መሳርያ የታጠቀ ሮቦት
በያዝነው ሳምንት ለእይታ የቀረበውና ጀርባው ላይ አልሞ ተኳሽ መሳርያ የተገጠመለት ባለ አራት እግር ሮቦት አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በጎስት ሮቦቲክስ አማካኝነት የተሰራው ይህ ታጣቂ ሮቦት በዚህ ሳምንት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በተካሄደው በአሜሪካን ጦር ኃይል ሕብረት አመታዊ ስብሰባ ላይ ነበር ለእይታ የበቃው፡፡ ሮቦቱ በጀርባው ስዎርድ ዲፌንስ በተባለው ተቋም የተሰራውና በሀገሪቱ ልዩ ኃይሎች ጥቅም ላይ የሚውለው ባለ 6.5 ሚ.ሜ አልሞ ተኳሽ መሳርያ የታጠቀ ሲሆን እስከ 1200 ሜትር ድረስ አርቆ መመልከት የሚችልና በቀንም ሆነ ምሽት የሚሰራ ካሜራም ተገጥሞለታል፡፡
ጎስት ሮቦቲክስ ከአውሮፓውያኑ 2015 አንስቶ ባለ አራት እግር ሮቦቶችን ሲሰራ የቆየ ሲሆን ከዚህ ቀደምም ፈንጂ የማምከን እና ሌሎች ተግባራትን ማከናወን የሚችሉ የዚህ ሮቦት አይነቶችንም ለእይታ አብቅቶ ነበር፡፡ ከነዚህ መካከል የአሜሪካን ጦር ኃይል ሙከራ እያደረገባቸው ያሉት ያልታጠቁ የሮቦቱ አይነቶች ይገኙበታል፡፡ ሮቦቶቹ ከፍተኛ የመንቀሳቀስ ብቃት ሲኖራቸው ለባለ ጎማ ሮቦቶች የሚያስቸግሩ አካባቢዎች ላይ ከመንቀሳቀስም ባሻገር በከፍተኛ ደረጃ ራስ ገዝ እንዲሆኑ ተደርገው የተሰሩ ናቸው፡፡ በዚህም ቀድሞ እንዲጓዙበት የተሰጣቸውን መንገድ ተከትለው በመሄድ በዚያ መንገድ ላይ ተቃራኒ ተዋጊ ኃይልም ሆነ ሌሎች ተግዳሮቶች ሲያጋጥሟቸው የማሳወቅ ስራን ይሰራሉ፡፡
ሆኖም እንደ ጎስት ሮቦቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጂረን ፓሪክህ ከሆነ አዲስ ይፋ የተደረገው ሮቦት እላዩ ላይ የተገጠመውን መሳርያ በራሱ ፈቃድ ሊተኩስበት አይችልም፡፡ ይልቁንም መሳርያውን የሚቆጣጠረው ሌላ ቦታ ያለ ባለሙያ ይሆናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ኩባንያው የሮቦቱን ምስል ይፋ ካደረገ በኋላ በርካቶች ጥርጣሬ እና ተቃውሞዋቸውን ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡ በአንዳንድ ባለሙያዎች ዘንድም ይህ በከፍተኛ ደረጃ የታጠቀ ሮቦት ለገዳይ ሮቦቶች መነሳት ማሳያ ተደርጎም እየተሰወደ ነው፡፡ ታድያ ከዚህ ቀደምም ባለ አራት እግር ሮቦቶች በህዝብ ዘንድ አሉታዊ እይታን ሲያስተናግዱ ቆይተዋል፡፡ ባሳለፍነው ሚያዝያ የኒው ዮርክ ፖሊስ ያልታጠቁ ባለ አራት እግር የሮቦት ውሻዎችን የመጠቀሙን ነገር ከፍተኛ ተቃውሞ ካጋጠመው በኋላ እርግፍ ሊተወው ተገዷል፡፡
ጂረን ፓሪክህ በበኩላቸው በተመሳሳይ መልኩ መሳርያ የታጠቁ ተሽከርካሪ ሮቦቶች ቢኖሩም ባለ አራት እግር ሮቦቶች ይህን ያህል ትኩረት ሊስቡ የቻሉት የእንስሳት አምሳል ያላቸው በመሆናቸውና ለበርካታ ዓመታትም ሳይንሳዊ ልብ ወለድ ፊልሞች የሮቦቶችን አደገኝነት ሲያሳዩ በመቆየታቸው ነው ይላሉ፡፡
የአሜሪካን ጦር ኃይል ሁሉም ሮቦቶች ላይ የሚገጠም መሳርያ በሰዎች ቁጥጥር ስር ሊሆን ይገባል የሚል ፖሊሲን ይከተላል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ሰዓት በተለይም ድሮኖች ኢላማቸውን እራሳቸው ለይተው ያለ ማንም ትዕዛዝ ጥቃት መፈፀም የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡
ምንጭ፤ ኒው ሳንቲስት እና ፊውቸሪዝም
ለተጨማሪ፤