ለሁለት አስርት አመታት ያገለገለውና ተጨማሪ 8 አመታት የሜቀሩት የአለማቀፉን ህዋ ምርምር ማዕከል መንኩራኩር መጨረሻ ምን እንደሚሆን ናሳ አስታውቋል።
ናሳ ባወጣው መግለጫ እንደሚለው ህዋ ላይ ሆኖ ምድርን እየዞረ የሚገኘው የአለማቀፉ የህዋ ማዕከል መንኩራክሩ (Internationa space station (ISS)) እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ አገልግሎት እንደሚሰጥና ከዛም በኋላ አገልግሎቱን ሲጨርስ ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ እንዲወድቅ እንደሚደረግ ገልጿል።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2000 ላይ ወደህዋ ከተላከ ጀምሮ ከምድር 365 ኪ.ሜ እርቆ ምድራችንን ሳያቋርጥ እየዞረ መረጃ የሚሰበስብ ሲሆን አስካሁን ቁጥራቸው 200 የሚደርሱ ከ 19 ሃገራት የተውጣጡ ሳይንቲስቶች (astronauts) መንኩራኩሩ ላይ ማረፍ ችለዋል።
የናሳ ሪፖርት እንዳለው በቀጣይ የግል የህዋ ምርምር ኩባንያዎች የሚልኳቸው መንኩራኩሮች ይህን የአለም አቀፍ የህዋ ምርምር ማዕከል የሆነውን መንኩራኩር ይተኩታል ይላል።

ይህ የምርምር ጣብያ የሆነ መንኩራኩር 2030 ላይ ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ኔሞ የተባለ ራቅ ያለ የውቅያኖሱ ክፍል ላይ እንዲያርፍ ይደረጋል ያለ ሲሆን ይህ ኔሞ የተባለው የውቅያኖሱ ክፍል ከ 1971 ጀምሮ ቁጥራቸው 263 የሚሆኑ የህዋ መንኩራኩሮች እና ሌሎች የህዋ እቃዎች አርፈዋል ።
በፈረንጆቹ ጃኑዋሪ ወር 2030 ላይ አሁን ምድርን ከሚዞርበት ኦርቢት ወጥቶ ወደምድር ጉዞ እንዲጀምር የማድረግ ሰራ ይከናወናል።
አለማቀፉ የህዋ ምርምር ማዕከል መንኩራኩር እስካሁን ምን ምን ስራዎችን አከናውኗል??
የአለምአቀፍ የህዋ ምርምር ማዕከል መንኩራኩር (ISS) ወደ ህዋ ከተላከ ጀምሮ የተለያዩ የሳይንስ ምርምሮችና የህዋ አሰሳዎች የሚካሄዱበት ላቦራቶሪ ሲሆን ይህ የህዋ ምርምር ማዕከል የሆነ መንኩራኩር ሙሉ ለሙሉ ተገንብቶ (ተገጣጥሞ ) ከተጠናቀቀ በፈረንጆቹ 2011 በኋላ ነበር ትኩረቱን ወደ ምርምር ያዞረው።
3000 የሚሆኑ የሳይንስ ምርምሮች ከ 108 ሃገራት የተሳተፉበት ሲሆን ምርምሮቹን የህዋ ሳይንስ ፣ የባዮሎጂ ፣ የሰውልጅ ስነልቦና ፣ የፊዚክስ ፣ የማቴሪያል ሳይንስ እና መንኩራኩሩ ላይ የመሬት ስበት ባለመኖሩ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ስራዎች ማሳያ እና ማስተማርያ ሆኗል።
በተጨማሪም የሰውልጅ አካል ያለ መሬት ስበት ምን ሊመስል እንደሚችል ማጥናት ተችሎበታል አንዲሁም መንኩራኩሩ ላይ ያለውን የውሃ ማጣርያ ዘዴ በመጠቀም ምድራችን ላይ ላሉ ቤቶች ውሃ እና አየርን የማጣራት ዘዴን አስተምሯል።
የመጀመርያው ህዋ ላይ የተካሄደው የ 3ዲ ህትመት ( 3D print ) በዚሁ እንኩራኩር ወስጥ ነበር እንዲሁም 5ኛ የቁስ አካላት መገኛ መንገድ ( state of matter ) የተገኘው በዚሁ መንኩራኩር ወስጥ ነው።

ሳይንቲስቶች በተጨማሪ በዚሁ መንክኩራኩር ውስጥ እጽዋትን ማሳደግ የቻሉ ሲሆን በዚህም ለወደፊት የራሳቸውን ምግብ እዛው መንኩራኩር ወስጥ ማምረት የሚችሉበትን ፍንጭ ሰጥቷል።
መኩራኩሩ ላይ የሚኖሩ ሳይንቲስቶች የራሳቸውን ጤንነውት የሚያጠኑ ሲሆን የመሬት ስበት በሌለበት የሰውልጅ እይታ እና አስተሳሰብ ላይ ያለውን ተጸእኖ እና የጡንቻዎች እና አጥንቶች መጠን እንደሚቀንስ ማስተዋል ተችሏል።
ቀጣይ አዲስ የሚተዋወቁ የህዋ ምርምር ማዕከል መንኩራኩሮች
በዚህ የአለም አቀፍ የህዋ ምርምር መንኩራኩር ላይ ብዙም ተሳትፎ ያልነበራት ቻይና የራሷን የህዋ ምርምር ጣብያ መንኩራኩር ህዋ ላይ መገንባት (መገጣጠም ) የጀመረች ሲሆን በያዝነው የፈረንጆች አመት መጨረሻ ላይ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ የጠበቃል።
በተመሳሳይ ሩሲያም አለማቀፉ የሀዋ ምርምር ጣብያ መንኩራኩር ላይ ያላትን ተሳትፎ አቋርጣ የራሷን ይህዋ ምርምር ማዕከል መንኩራኩር ሰርታ በ 2030 ላይ ወደህዋ ለመላክ አቅዳለች።

በመጨረሻም አለማቀፉ የህዋ ምርምር ማዕከል (ISS) በ 3 ምዕራፎች ተከፍሎ ተልእኮውን እየፈጸመ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን 2ቱን መዕራፎች አጠናቆ ወደ 3ኛው ምዕራፍ አጋማሽ እየተንደረደረ ሲሆን በፈረንጂኦቹ 2030 ላይ የመንኩራኩሩ ፍጻሜ ሊሆን ቀን ተቆርጧል።