በቴክኖሎጂው ዓለም ሰሞኑን መነጋገሪያ ከሆኑ ዜናዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የሮቦቶች አምራች ኩባንያ የሆነው ፕሮሞቦት ለሚሰራቸው ሮቦቶች የፊት ገፅታ እና ድምፅ ለመግዛት ማስታወቂያ አስነግሯል፡፡
ፕሮሞቦት ዋና መቀመጫውን በራሺያ ያደረገ ሰው መሰል ሮቦት (humanoid robot) አምራች ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው በአውሮፓውያኑ 2023 ወደ ስራ ለሚገቡ ሮቦቶች ምርት ግብዓት እንዲሆነኝ ፊትዎን እና ድምፅዎን ሁለት መቶ ሺ ዶላር ከፍዬ ለዘላለም ልጠቀምበት ማለቱን ኒውስዊክ ዘግቧል፡፡
ደግ እና ወዳጃዊ ፊት ያላቸው የትኛውም እድሜ፣ የቆዳ ቀለም እና ጾታ ባለቤቶች ማመልከት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
የሮቦቶቹን የፊት ገፅ እና ቀሪ አካላቸውን የማልበስ ሂደት የሚከናወነው የአመልካቾቹን ፊት እና አካል በ3ዲ ቅርፅ በመውሰድ እንደሆነ ዘገባው አትቷል፡፡ ድምጻቸውም ከአመልካቹ በሚቀዳ የመቶ ሰዓት ንግግር ተመስርቶ እንደሚዋቀር ተብራርቷል፡፡
ሮቦቶቹ በሆቴሎች፣ በገበያ ማዕከላት እና አየር መንገዶች አገልግሎት እንዲሰጡ ታቅዶ የሚሰሩ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
Yes