ባርድ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ቻትቦት በማንኛውም ጉዳይ ዙሪያ ከሰዎች የሚቀርብለትን አጭር ጥያቄ በመቀበል አስፈላጊውን ማብራሪያ መስጠት እንደሚችል ታውቋል፡፡
በዚህም ዲፕ ለርኒንግ የተባሉትን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስልተቀመሮች በመጠቀም የተማረውን ከፍተኛ መጠን ያለው ዳታ መሠረት አድርጎ እንደ ጽሁፍ ወይም ምስል ያሉ ይዘቶችን መለየት፣ ማጠቃለል፣ መተርጎም፣ የመተንበይ እና የማመንጨት አቅምን የተላበሰ ነው፡፡
ባርድ ስፋት ያለውን የዓለም እውቀት፤ አስተውሎት እና ፈጠራን ካጣመሩ የኩባንያው ግዙፍ የቋንቋ ሞዴሎች ጋር በማዋቀር እንደሚሰራ የጉግል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳንዳር ፒቻይ ተናግሯል፡፡
ቻትቦቱ የተገነባው ላምዳ በሚል መጠሪያ በሚታወቀው የኩባንያው የቀደመ አነጋጋሪ መተግበሪያ ላይ መሠረት አድርጎ መሆኑን ቢ.ቢ.ሲ ዘግቧል፡፡
የጉግል ቻትቦት ባሳለፍነው የአውሮፓውያኑ ዓመት መጨረሻ ኦፕን ኤ.አይ በተባለው ኩባንያ ይፋ የተደረገውን ቻት ጂ.ፒ.ቲ የተባለ ከፍተኛ አቅም ያለው ተመሳሳይ መተግበሪያ ጋር እንደሚፎካከር ይጠበቃል፡፡