
እስቲ ለአንድ አፍታ አስቡት… በጭንቅላታችሁ ውስጥ ያለውን ምርጥ የቢዝነስ ሀሳብ ወይም አፕሊኬሽን፣ ምንም አይነት የኮምፒውተር ኮድ መጻፍ ሳያስፈልጋችሁ፣ በቀላሉ በፅሁፍ በመግለፅ ብቻ ወደ እውንነት መቀየር ብትችሉስ? “የምፈልገው ደንበኞቼ ቀጠሮ የሚይዙበት፣ ክፍያ የሚፈፅሙበት እና መልዕክት የሚላላኩበት አፕሊኬሽን ነው” ብላችሁ ስትነግሩት፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) በደቂቃዎች ውስጥ ሙሉ አፕሊኬሽኑን ሰርቶ ቢያቀርብላችሁስ?
ይህ የሳይንስ ልብወለድ ይመስላል አይደል? ነገር ግን እውን እየሆነ ያለ እና ዓለምን በፍጥነት እየቀየረ ያለ እውነታ ነው። የዚህ እውነታ ትልቁ ማሳያ ደግሞ የእስራኤላዊው ወጣት፣ ማኦር ሽሎሞ ታሪክ ነው።
የአንድ ወጣት ህልም እና የ80 ሚሊዮን ዶላር ታሪክ
ማኦር ሽሎሞ፣ የ31 ዓመት ወጣት የሶፍትዌር ገንቢ ነው። በውስጡ ትልቅ ሀሳብ ነበረው፤ “ቴክኒካዊ እውቀት የሌላቸው ሰዎች ሳይቀሩ የራሳቸውን ሶፍትዌር በቀላሉ እንዲሰሩ ማድረግ!” ይህንን ህልሙን እውን ለማድረግ ቤዝ44 (Base44) የተባለ ኩባንያ አቋቋመ።
የሚገርመው፣ ይህንን ኩባንያ የጀመረው ከባለሀብቶች ሳንቲም ሳይቀበል፣ በራሱ አቅም ነበር። ኩባንያው ስራ ከጀመረ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ያሳየው እድገት ማመን የሚያዳግት ነበር፦
- በ3 ሳምንታት ውስጥ ብቻ 10,000 ተጠቃሚዎችን አፈራ።
- በ6 ወራት ውስጥ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር 250,000 ደረሰ።
- ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውን የAI ቴክኖሎጂ እየተጠቀመም ትርፋማ መሆን ቻለ።
ይህንን አስደናቂ እድገት የተመለከተው ታዋቂው የዌብሳይት መስሪያ ኩባንያ ዊክስ (Wix)፣ ቤዝ44ን በያዝነው ሳምንት በ80 ሚሊዮን ዶላር (ከ9 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ) በጥሬ ገንዘብ ገዝቶታል። ይህ ሁሉ የሆነው ገና የስድስት ወር ብላቴናነት ደረጃ ባለ ኩባንያ ላይ ነው! ምንም እንኳን ሽሎሞ አብረውት በስራው የተሳተፉ ሌሎት አምስት አብረው የመሰረቱ ቋሚና ሁለት ተቀጣሪዎች ቢኖሩትም፣ ይህ ታሪክ የአንድ ሰው ሀሳብ እና ቁርጠኝነት በቴክኖሎጂ ታግዞ ምን ያህል በፍጥነት ወደ ትልቅ ስኬት ሊለወጥ እንደሚችል ማሳያ ነው።
“ሀሳብን ወደ ሶፍትዌር” የሚቀይረው አስማታዊ ቴክኖሎጂ
የሽሎሞ ኩባንያ የተሳካለት “ቫይብ ኮዲንግ” በሚባለው አዲስ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ነው። ይህ ማለት ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን አይነት አፕሊኬሽን በጽሁፍ ሲገልፁለት፣ ከጀርባ ያለው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ሙሉውን ስራ ማለትም ከመረጃ ቋት (database) እስከ ክፍያ ሲስተም ድረስ ያለውን ሁሉ ይገነባል። ይህ ቴክኖሎጂ ለዓመታት የኮዲንግ ትምህርት ሳያስፈልግ፣ ማንኛውም ሀሳብ ያለው ሰው ከመሬት ተነስቶ የራሱን ቴክኖሎጂ እንዲፈጥር ያስችለዋል።
ታዲያ የዚህ ወጣት ታሪክ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ምን ይነግረናል?
ይህ ታሪክ ሩቅ አገር ላይ የሆነ የአንድ ግለሰብ የስኬት ወሬ ብቻ አይደለም። ይልቁንም በዓለማችን ላይ እየተከሰተ ላለው ታላቅ የቴክኖሎጂ አብዮት ትልቅ ማሳያ እና ለኛ ኢትዮጵያኖችም ትልቅ እድልን ይዞ የመጣ ነው።
- የጨዋታው ህግ ተቀይሯል፦ ከዚህ በፊት የሶፍትዌር መተግበሪያ ለመስራት የብዙ ዓመታት የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት እና ልምድ ይጠይቅ ነበር። አሁን ግን እንደ ቤዝ44 ያሉ ቴክኖሎጂዎች ይህንን እንቅፋት እያፈረሱት ነው። ዋናው ነገር ሀሳብ እና ችግር ፈቺ እይታ እንጂ የኮዲንግ እውቀት ብቻ አይደለም።
- የእኛ ወጣቶች እና ሀሳቦቻቸው፦ ኢትዮጵያ በፈጠራ እና በሀሳብ በተሞሉ ወጣቶች የታደለች ናት። በየሰፈሩ፣ በየከተማው ያሉ ችግሮችን የሚፈቱ ስንት ሀሳቦች በወጣቶች ጭንቅላት ውስጥ አሉ? ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ እነዚህን ሀሳቦች ከጭንቅላት አውጥቶ ወደ እውነተኛ፣ ምናልባትም ትርፋማ ወደ ሆነ ቢዝነስ ለመቀየር የሚያስችል ድልድይ ነው።
- ትምህርት ቤት በጃችን ነው፦ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ለመማር የግድ ዩኒቨርሲቲ መግባት አያስፈልግም። ዩቲዩብ፣ ነፃ የኦንላይን ኮርሶች እና የተለያዩ ድረ-ገጾች የእውቀት ማዕከላት ሆነዋል። የሚጠበቀው ፍላጎት እና ቆራጥነት ብቻ ነው። ሩቅ ሳትሄዱ በETN LEARN ስር ለተጠቃሚዎች ይፋ የሆነውና በውጪ ገበያ ወደ1500 የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣውን የቫይብ ኮዲንግ ሙሉ የሁለት ወር ስልጠና በ1500 የ$ETN ሳንቲሞች [ወደ 1500 የኢትዮጵያ ብር ገደማ] ብቻ በማውጣት ሊያውም በራሳችን ቋንቋ እና አስተማሪዎች በቀላሉ መማር እንደሚቻልም ልብ ይሏል።
ከየት እንጀምር?
ይህንን ስታነቡ “እኔስ እንዴት የዚህ አካል መሆን እችላለሁ?” ብሎ መጠየቅ አይቀሬ ነው። መልሱ ከምናስበው በላይ ቀላል ነው፦
- መሞከርና ማሰስ (Explore)፦ እንደ Wix, Bubble, Adalo ወይም ሌሎች “No-Code/Low-Code” የሚባሉ ፕላትፎርሞችን በነፃ መሞከር ጀምሩ።
- መስኩን በትምህርት ማበልፀግ፡- በዘርፉ ያለውን እንቅስቃሴ እና ጥቅሞች መለየት እና ከውስጣችሁ ምን መስራት እንደምትችሉ ሀሳቦቻችንሁን ከማዋቀራችሁ፤ ከማሰባችሁ እና በዛም ሀሳባችሁ ላይ ውሳኔን ከማሳፈላችሁ በፊት በትክክለኛ የኦንላይን ትምህርት ለመደገፍ እና ለመብቃት ጥረት ለማድረግ ሞክሩ። ይህንንም በተለይ አቅሙ ላለው ከላይ የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን ከፍሎ ማግኘት ቢችልም በተቻለ ግን ወይ እጅግ አነስተኛ በሚባል ዋጋ ትምህርቱን ከሚሰጡ ታማኝ ምንጮች መውሰድ አልያም ነፃ የኦንላይን ትምህርቶችን በማነፍነፍ ማሳካት የምትችሉ ይሆናል።
- ችግር ፈልጎ መፍታት፦ ትልቅ ነገር ከማሰብ በፊት፣ በዙሪያችሁ ያለን ትንሽ ችግር ለመፍታት ሞክሩ። ለምሳሌ፣ በሰፈራችሁ የሚገኝን መለሰተኛና ለአቅመ ኦንላይን የደረሰ ሱቅ ምርቶቹን ኦንላይን እንዲያሳይ የሚረዳ ቀላል ዌብሳይት ወይም አፕ ለመስራት ሞክሩ። ወይም ሌላ በአካባቢያችሁም ሆነ በአጠቃላይ በአገሪቱ ባሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ያሉ ክፍተቶችን በመመልከት በእነዚያ ክፍተቶች ላይ የተመረኮዙ እና መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ መነሻ ሀሳቦችን በተቻለ ለማሰብ ሞክሩ።
- መተባበር፦ ሽሎሞ ብቻውን አልነበረም። ከጓደኞቻችሁ ጋር ተሰባሰቡ፣ ሀሳብ ተለዋወጡ፣ መሰል አስተሳሰብ ያሏቸው ወጣቶች በሚገኙባቸው ኮሚዩኒቲዎች እና የኦንላይን ግሩፖች ላይ ወዳጅነቶችን በመመስረት በጋራ መስራትን ተለማመዱ።
- መማርን አታቁሙ፦ ይህ ቴክኖሎጂ በየቀኑ እየተለወጠ ነው። አዳዲስ ነገሮችን ለመማር እና ራሳችሁን ለማሳደግ ሁሌም ዝግጁ ሁኑ።
የማኦር ሽሎሞ ታሪክ የሚያሳየን አንድ ትልቅ እውነት አለ፦ ዛሬ ላይ ትልቅ ካፒታል ወይም የብዙ ዓመታት ልምድ ሳይሆን፣ አንድ ምርጥ ሀሳብ፣ ቁርጠኝነት እና ትክክለኛውን የቴክኖሎጂ መሳሪያ መጠቀም የአንድን ሰው ህይወትና የዓለምን ገፅታ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መቀየር እንደሚችል ነው።
ቀጣዩ የሚሊዮን ዶላር ሀሳብ በእርስዎ ጭንቅላት ውስጥ ሊሆን ይችላል። ቴክኖሎጂው እጃችን ላይ ነው፤ ጊዜው ያለምንም ጥርጥር አሁን ነው። በዚህም በተቻለ በAI እና በቫይብ ኮዲንግ ዙሪያ ያላችሁን እይታና ቸልተኝነት ወደኋላ መለስ ብላችሁ በማጤን ለጉዳዩ አስፈላጊውን ትኩረት ትሰጡት ዘንድ ለማስታወስ እንወዳለን።