ክፍል አንድ
ለመሆኑ ቢትኮይን ምንድነው? በዚህ ልክ በዓለም ዙሪያስ እንዴት መነጋገሪያ ሊሆን ቻለ? በዚህ አምድ በተከታታይ ክፍሎች ይህንን አዲስ የፋይናንሳዊ አብዮት እና የቴክኖሎጂ እመርታ ስረ መሰረት እና መሰረታዊ ምንነት ጠለቅ ባለ እና ለአረዳድ ምቹ በሆነ መልኩ የሚቀርብ ይሆናል።
Magic. Internet. Money. አስማት፤ ኢንተርኔት፤ ገንዘብ!!!
በሌላ አጠራሩ ቢትኮይን። ለመሆኑ ከእነዚህ መገለጫዎችም በላይ የተባለለት አለምን እያነጋገረ ያለና በስራ ላይ ያለውን ባህላዊውን የማእከላዊ የባንክ ስርዓት እና የካሽን ስርዓት ይተካል የሚባልለት ይህ የምናባዊ መገበያያ ምንድነው? ስለምንስ መነጋገሪያ እና የብዙሀንን ትኩረት ሳቢ ሊሆን ቻለ? በዚህ አጭር ፅሁፍ ይህንን የዲጂታል መገበያያ መሰረታዊ ምንነት፤ ጥቅም፤ ትግበራ እና መሰለ ሁነቶች ሁሉ ለመዳሰስ ይሞከራል። በፅሁፉ ይህንን አብዮታዊ የተበያለለት የግብይት ስርአት ከስረ መሰረቱ በጠለቀ መልኩ አንባቢያን የሚረዱት ይሆናል። በዚህም ለብዙሀን “ተስፋ” የተባለለትን በአሁኑ ሰዓት በአለም ዙሪያ በሚሊዮኖች እየተነጋገሩበት እውቀታቸውንም እያሰፉበት ስላለ አዲስ የቴክኖሎጂ እመርታ ግልፅ በሆነ መልኩ የምትረዱት ይሆናል። መልካም ንባብ።
የመጀመሪያው መጀመሪያ ፡ ቢትኮይን እንዴት ተጀመረ?
እኤአ ጃንዋሪ 3 2009 ዓ/ም ማንነቱ እስካሁን በውል ያልታወቀ ነገር ግን እጅግ በጣም የመጠቀ እሳቤ ያለው ሳቶሺ ናካሞቶ የተባለ ግለሰብ ምናልባትም የግለሰቦች ስብስብ ቢትኮይን የሚለውን የምናባዊ መገበያያ ዘዴ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ህዝብ አስተዋወቀ።
ይህ ግለሰብ ወይም የግለሰቦች ስብስብ ማንም ይሁን ማን ግን ይኸው ለአለም ህዝብ በነፃ የተዋወቀ የቴክኖሎጂ እመርታና የአለም የመጀመሪያው የሰመረ እና በትክክለኛው መንገድ መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ የሆነ የምናባዊ መገበያያን ለአለም በማበርከት የምናውቀው አለማዊ ነገር ሁሉ በሌላ ዕይታ እንዲታይ መንገድ የከፈተ ሊሆን በቅቷል። በግርድፉ ስንተረጉመው፤ ቢትኮይን [Bitcoin – በእንግሊዘኛ ቋንቋ በካፒታል የB ፊደል የሚጀምረው እና ስምን የሚገልፀው ቃል] ማለት አለም አቀፍ የሆነ፤ ምንም አይነት የአገራት መካለል የማይበግረው፤ በየትኛውም የአለም ክፍል ላይ ዲጂታል መጠቀሚያ ቁስ እና የኢንተርኔት መስመር እስካለ ድረስ ተደራሽነቱ የተረጋገጠ ኢ-ማእከላዊ ፕሮቶኮል ሲሆን በተለየ ሁነት የአቻ ለአቻ ግብይቶችን ወይም የገንዘብ ልውውጦችን በቢትኮይን ምናባዊ መገበያያ ወይም ክሪፕቶከረንሲ [bitcoins – በእንግሊዘኛው ትንሿ “b” ፊደል መነሻነት የሚፃፈው] አማካኝነት ማድረግ እንዲቻል የሚያደርግ እና ከጅምሩ የማይለዋወጥ የኮይኖች አቅርቦት ኖሮት የተነሳ ይኸው የኮይኖች ህትመት ወደገበያው የሚገባበት ሁነት ደግሞ በየጊዜው እየቀነሰ እንዲሄድ ተደርጎ የተሰራ የግብይት መረብ ነው።
ይህም ማለት ቀለል ባለ አቀማመጥ በቢትኮይን ከረንሲ በመጠቀም ገንዘባችንን በአለም ዙሪያ ላለ ማንኛውም ግለሰብ፤ የትም ይሁን የት ካለምንም ሶስተኛ አካል ጣልቃ ገብነት መላክ የሚያስችል ስርዓት ነው ማለትም ይቻላል።
ቢትኮይን እውነት ለመናገር ምንም አይነት ፈጠራዊ እሳቤን ይዞ የመጣና አላማው አድርጎ የተነሳ የግብይት መረብ አይደልም። ይልቅስ ዓለም ላይ ካለው ነባራዊ እውነት በመነሳት በስራ ላይ ያለውን ትክክለኛ ያልሆነ፤ ለሁሉም ተደራሽነቱ ጥያቄ ውስጥ ያለውን እና እጅጉን በዋጋ ግሽበት የሚፈተነውን ባህላዊውን የፋይናንስ ስርዓት ለማሻሻል እና ለህዝቦች የፋይናንስ ነፃነትን ለመስጠት አልሞ የተነሳ የግብይት መረብ እና የምናባዊ ግብይት ማካሄጃ ስርዓት ነው። የፋይናንስ ስርዓቱን ኢ- ማእከላዊ በማድረግ እጅግ ውስብስብ የሆነውን እና በአለም ዙሪያ ከ2 ቢሊዮን በላይ ቁጥር ያለውን ህዝብ ያላማከለውን ስርዓት የሚተካ እንዲሁም ተዓማኒነቱ እና ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ያለማንም ሶስተኛ ወገን አዛዥነት እና አስፈላጊነት ማንም ግለሰብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓትም ጭምር ነው።
ቢትኮይን ያመጣው መፍትሄ ታዲያ ምንድነው?
ይህንን ሁነት በተለያዩ መንገዶች ከፋፍለን መመልከትና ቢትኮይን ተፅእኖ አርፎባቸዋል የተባሉ ዋና ዋና ሁነቶች ለየብቻ ለማየት እንሞክር።
ማእከላዊነት: ቢትኮይን ከምንም በላይ ማእከላዊ የሆነውን እና እንደባንክ የመሳሰሉ ሶስተኛ ወገኖች የሚያስገልጉበትን ስርዓት የሚቀይር የግብይት ስርዓት ሆኖ እናገኘዋለን። በተለይም እነዚህ እንደክሪዲት ካርድ ኩባንያዎች እና ማእከላዊ ባንኮች ያሉ አካላት የምናደርገውን ግብይት እና የገንዘብ ልውውጥ ካላረጋገጡልን አልያም ግዴታ በእነዚህ ሶስተኛ ወገኖች ተቀባይነት እስካላገኘ ድረስ ማንኛውም ግለሰብ የእነዚህኑ ሶስተኛ አካላት እሺታ እና አረጋጋጭነት እንዲያስፈልገው ተደርጎ የተቀረፀው የአለም የፋይናንስ ስርዓት በአለም ዙሪያ ከ2 ቢሊዮን በላይ ቁጥር ያለውን ህዝብ አለማማከላቸው እጅግ የበዛ ጥያቄው ያልተመለሰ የማህበረሰብ ክፍል እንዳለ አመላካች ከመሆኑ አንፃር የቢትኮይን አስፈላጊነት ለነዚህ ሁሉ ሰዎች መልስ የሚሆን ሆኖ እናገኘዋለን። በዚህም አሁን ባለው የፋይናንሳዊ ስርዓት ያስፈልጉ የነበሩ ሶስተኛ አካላትን በመተካት ቢትኮይን ሰዎች አቻ ለ አቻ በሆነ ሁነት ማእከላዊ የሆነ አረጋጋጭ አካል ሳያፈልግ እርስ በእርስ እምነት ጥለው ግብይቶቻቸውን እና የገንዘብ ዝውውሮቻቸወን እንዲያከናውኑ ያደረገ የግብይት መረብ ሆኖ እናገኘዋለን።
ከማጭበርበር የፀዳ እና የማረጋገጫ መንገዱ ፍፁማዊነት፡ ቢትኮይን በፊያት መገበያያዎች ላይ ልንመለከተው ያልቻልነውን በክፍልፋዎች የሚገኙ ግብይቶችንም ጭምር ማረጋገጥ የሚችል የግብይት ስርዓት ሲሆን አለፍ ሲልም የማጭበርበር ሁነቶችን ለማከናወን ከቶውንም የማይቻልበት ስርዓት ነው። ለምሳሌ እጅግ የበዙ ፎርጂድ የዶላር ቢሎች በገበያ ውስጥ እንዳሉ ይታወቃል። ዳታዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በአለም ገበያ ላይ እየተዘዋወሩ ከሚገኙ የአሜሪካን ዶላር ቢሎች ከ10ሺው አንዱ ፎርጂድ መሆኑን የአሜሪካ ትሬዠሪ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል። ይህንን ሁነት ደግሞ አማካይ የሰው ቁጥር ፎርጅዱን ከትክክለኛው መለየት የማይችል በመሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢና አስቸጋሪ ሲያደርገው ተመልክተናል። በግልባጩ ግን ማንም ሰው ተመሳስለው የተሰሩ ቢትኮይኖችን መፈብረክ ወይም ማተም አይችልም። ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ቢትኮይን የተመሰረተበት እና የሚዘወርበት ብሎክቼይን የተባለ ስነ-መሰውራዊ [cryptographical] ስርዓት ለሁሉም ተጠቃሚ ግልፅ በሆነ መንገድ የሚታይ እና ምንም አይነት የተሳሳተ የቢትኮይን መገበያያ ዲጂታል ኖቶች እንዳይኖሩት የሚያደርገው በመሆኑ ነው።
የዋጋ ግሽበት: የቢትኮይን መረብ በአጠቃላይ 21 ሚሊዮን የቢትኮይን ዲጂታል ከረንሲዎችን ብቻ እንደሚያትም ፕሮግራም ተደርጎ የተነሳ የዲጂታል የመገበያያ መረብ ነው። ከ21 ሚሊዮን በላይ ቢትኮይኖች መቼም ሊፈጠሩ አይችሉም ማለት ነው። ልክ የፌደራል ሪዘርቭ ኢኮኖሚውን ለማስተካከል ዶላር እንደሚያትመው አልያም የየትኛውም አገራት ማእከላዊ ባንኮች ሲያስፈልጋቸው በገበያው ውስጥ ብር እንደአዲስ አትመው እንደሚያስገቡበት ሁነት በቢትኮይን ስርአት ከ21 ሚሊዮን በላይ ቢትኮይኖች ወደገበያ የሚገቡበት አንዳችም ሁነት አይኖርም። ይህ ደግሞ በተለይም ከዚሁ ብርን እያተሙ ወደኢኮኖሚው ከሚያስገቡት የአለም አገራት ታሪክ አንፃር ሰዎች ያላቸው የገንዘብ መጠን የመግዛት አቅሙ እየቀነሰ ሊሄድ አይችልም ማለት ነው። አለፍ ሲልም የቢትኮይን ተጠቃሚ በጨመረ ቁጥር አቅርቦቱ አነስተኛ ከመሆኑ አንፃር እና እስከ 8 ዲጂቶች ድረስ መከፋፈል መቻሉ በየጊዜው ያለው ዋጋ የመጨመሩን ሁነት አመላካች ነው። ባለፈው መቶ አመት ብቻ ከ98 በመቶ በላይ የመግዛት አቅሙን ካጣው የዶላር ስርዓት አንፃር እንኳን ብንመለከተው ቢትኮይን ከተጀመረበት 2009 አንስቶ ምንም አይነት ሞኒተሪ ቫሊዩ ካለመኖር ተነስቶ እስከ 69 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ከተሸጠበት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ይኸው ከአቅርቦቱ ማነስ እና የተወሰነ መሆን ጋር በተያያዘ ያለው የዋጋ ግሽበት የመቋቋም ሀይሉ ነው።
በእርግጠኝነት ለቢትኮይን እና ብሎክቼይን እሳቤ አዲስ የሆነ የዚህ ፅሁፍ አንባቢ የሚከተለው መደናገር በጭንቅላቱ እንደሚመጣ ይታመናል።
“ከላይ ያልሽው አንድም ነገር አልገባኝም!!!” የሚል።
እውነት ለመናገር መደናገራችሁም ሆነ ጥያቄያችሁ ትክክለኛ እና ስህተትም የሌለበት ነውና ብዙም ግር አትሰኙ። እንደብሎክቼይን፤ ኢማእከላዊነት እና ስነመሰውራዊ ስርዓት የተባሉ ፅንሰሀሳቦች ሁሉ በዚህ የገለፃ ደረጃ ላይ አደናጋሪ መሆናቸው ተጠባቂ ነው። ይሁንና በዚሁ ፅሁፍ በተከታታይነት በሚቀርቡት ሀሳቦች ላይ በጥልቀት ስለሚዳሰሱ ያን ያህል ግር አይበላችሁ። ለሚኖሩት ጥያቄዎችም በተቻለ ስለእያንዳንዳቸው በጠለቀ መልኩ ለመዳሰስ ይሞከራል። እውነታው በዚህ ደረጃ ላይ ሆነን ስለቢትኮይን ቴክኒካዊ እሳቤዎች በጥልቀት ማወቁ ያን ያህል አስፈላጊ ያልሆነና ምናልባትም አንድ በአንድ በሰከነ መልኩ ትንታኔ ካልተሰጠባቸው አደናጋሪነታቸው የሚጨመር መሆኑ ነው። ይሁንና ግን ቢትኮይን ምርጥ የቴክኖሎጂ እመርታ ነው ብቻ ስለተባለና ስለሚተገበርበት ሁነት ጥያቄ ማንሳታችሁ ተገቢና ምክንያታዊም ጭምር በመሆኑ ትክክለኛነታችሁን ሳላረጋግጥ ማለፍ አልፈልግም። በአጠቃላይ ቢትኮይን በተለይም ለአረጋጋጭነት እና ለተዓማኒነት የሚያስፈልጉ የነበሩ ነገር ግን ከጊዜ፤ ከገንዘብ እና ከተደራሽነት አንፃር ብዙ ጥያቄዎች ያሉባቸውን የሶስተኛ ወገን የፋይናንስ አካላት አላስፈላጊነት ያረጋገጠ እና ሰዎች እነዚህ አካላት ሳያስፈልጉዋቸው በየትኛውም የአለም ክፍል ሆነው በደቂቃዎች የትኛውንም መጠን ያለው ገንዘብ እንዲላላኩ፤ እንዲገበያዩ አልይያም እንዲለዋወጡ የሚያደርግ የፋይናንስ ስርአት ነው።
በጭንቅላታችሁ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጥያቄዎች አሁንም ሊጨምሩ እንደሚችሉ እገምታለው።
“ግን… እንዴት ማእከላዊ የሆነ አስተማማኝ እና አረጋጋጭ አካል ሳይኖር እምነቴን ላኖር እችላለው? ቢርኮይን አንድ የስካም አይነት እና ከዚህ በፊት እንዳየናቸው የፋይናንሳዊ ማጭበርበሪያ መንገዶች ስላለመሆኑስ በምን እርግጠኛ ልሆን እችላለው? እንደሚባለውስ ቢትኮይን በአንድ ጊዜ ባለፀጋ የሚያደርገኝ ምናባዊ መገበያያ ነው? የቢትኮይን ትክክለኛ ዋጋስ [intrinsic value] ምን ያህል ነው? ቢትኮይንንስ የሚያስተዳድረው አካል ማነው?
እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች በሀሳቦቻችሁ ከመጡ በጣም ትክክለኛ እና መሰረታዊ አለፍ ሲልም አመንክዮ ላይ የተመሰረቱ የአንድ ምክንያታዊ ግለሰብ ጥያቄዎች ናቸው። በተቻለም በሂደት ስለእያንዳንዱ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥባቸው ሲሆን ለአማርኛ አንባቢያን ምቹ እና ለመረዳትም ቀላል ይሆኑ ዘንድ ደረጃ በደረጃ ትንተና የሚሰጥባቸው ይሆናል። በተከታታይ በዚህ አምድ ላይ በሚቀርቡ ፅሁፎችም ስለቢትኮይን መሰረታዊ ምንነት፤ ስላለው አጠቃላይ ቴክኒካዊ አሰራር እና ቴክኖሎጂያዊ ቁመና እና በዋናነትም በተግባራዊነቱ እና በሚሰራበት ሁነት ላይ ጠለቅ ያሉ ዳሰሳዎችን የምናደርግ ይሆናል። በዚህም በቀጣይ በተከታታይ ክፍሎች በሚቀርቡ የዚህ ክፍል ተቀጣይ ሀቲቶች ውስጥ እንዴት የመጀመሪያ የቢትኮይን ልውውጣችሁን ማድረግ እንደምትችሉ ከሚያሳይ ትንታኔ እስከ ቢትኮይን በአለም ዙሪያ እንዴት የፋይናንሳዊ ነፃነትን ለሚሊዮኖች እየሰጠ እንዳለ የምንዳስስ ይሆናል። በቀጣይ ክፍል በተለይም የቢትኮይን የግብይት ሁነት ስለሚዘወርበት የቢትኮይን የብሎክቼይን የመዝገብ አያያዝ ስርዓት ምንነት እና ትግበራ የምንመለከት ይሆናል።
የቢትኮይን ብሎክቼይን ስርዓት
በእርግርጥም እንደአንድ የብሎክቼይን ቴክኖሎጂ አድናቂ እናንተም ስለዚህ የፋይናንሳዊ አብዮት በጥልቀት በምትረዱበት ወቅት እጅጉን እንደምትገረሙ እርግጠኛ ነኝ። ብሎክቼይንን እና ተግባራዊ የሚሆንበትን ሁነት መረዳት እጅጉን አሰልቺ፤ ግራ አጋቢ እና አስቸጋሪ ቢመስልም መሰረታዊ ምንነቱን በቀጣታ ከስሙ ግርድፍ ትርጉም መረዳት ግን ያን ያህል ከባድ አይሆንም።
አዎ፤ ቃል በቃል ብሎክቼይን ማለት ከእንግሊዘኛ ቃሉ ቀጥተኛ ትርጓሜ ጋር የተያያዘ ነው። Block እና Chain ከሚሉት ሁለት የእንግሊዘኛ ቃል የተፈበረከ የቃሎች ውህድ ማለት ነው። ትርጓሜውም ለሁሉም ተጠቃሚ በግልፅ በሚታይ መልኩ የተቀመጠ የውሂቦች ስብስብ ሲሆን ይኸው የዳታዎች ስብስብም የተቀመጠው እርስ በእርሳቸው በተያያዙ ዲጂታል ብሎኮች ነው። በቀላል አማርኛ ልክ ባንኮች የተለያዩ የብር እንቅስቃሴዎችን የሚይዙበት ማህደር የተቀጣጠሉ ገፆች በአንድ ላይ ተያይዘው እንደተቀመጠው ሁሉ በብሎክቼይን ስርዓቱ ደግሞ የቢትኮይን ግብይቶች/ዝውውሮች የሚመዘገቡበት ይሆናል። የዚህን የተመዘገበ ዳታ ትክክለኝነት የሚያረጋግጡ በቢትኮይን ሶፍትዌሩ የሚዘወሩ ኮምፒዩተሮች በመላው አለም እያንዳንዱ የቢትኮይን ዝውውር በሚደረግበት ቅፅበት ምንም ልዩነት ሳይኖረው ይመዘገብባቸዋል ማለት ነው። በዚህም ከጅማሬው 2009 ጀምሮ የነበሩ የቢትኮይን ዝውውሮች ሁሉ በአንድ ላይ ለሁሉም ግልፅ በሆነ መንገድ በዚህ ብሎክቼይን ብለን በምንጠራው ዲጂታል መዝገብ ላይ ተመዝገበው የሚቀመጡ እና መመዝገባቸውም የሚቀጥል ይሆናል። ተያይዞም በነባራዊ ምሳሌ ለማቅረብ ያህል ባንኮች የተጠቃሚዎቻቸውን የገንዘብ ዝውውር በየእለቱ በመመዝገብ ሂደት እስካሁን ያላቸውን እንቅስቃሴ በየእለቱ ዝውውሮቹ በተደረጉ ቁጥር እየመዘገቡ በዳታቤዛቸው ላይ እንደሚያስቀምጡት በብሎክቼይንም ላይ ይኸው የዝውውር ምዝገባ ይካሄዳል። ባንኮቹ ዝውውሮችን በመመዝገብ ሂደት አንድ ገፅ ላይ ያሰፈሯቸው ዝውውሮች ገፁን ሲሞሉት ወደሌላ ገፅ እንደሚሄዱት ሁሉ በብሎክቼይን መረብ ውስጥም አንድ ብሎክ ላይ የተመዘገቡ የቢትኮይን ዝውውሮች ብሎኩን ሲሞሉት ወደቀጣይ ብሎክ በመሄድ ዝውውሮችን መመዝገብ ይቀጥላል ማለት ነው።
በብሎክቼይን ስርአት ውስጥ ግን ዝውውሮቹ የተረጋገጡ እና ደህንነታቸውም በስነ መሰውራዊ ስሌት የተጠበቀ በመሆኑ ዝውውሩን ከሚያካሄዱት ሁለት ግለሰቦች ውጪ የሚያስፈልግ ተጨማሪ አረጋጋጭ ሶስተኛ አካል የሌለ እና ለሁሉም ተጠቃሚ በግልፅ የሚታየው የብሎክቼይን መዝገብ እስካለም ደህንነቱ የተረጋገጠ እና ከማጭበርበር የፀዳ ግብይት/ዝውውርን ማድረግ የሚችል ይሆናል።
ቢትኮይን በእርግጥም ጠንካራ የግብይት መሳሪያ ነው
አሁን ላይ ያለው አለም አቀፉ የፋይናንስ ስርዓት በጥልቀት እየተፈረካከሰ ለመሆኑ ማስረጃ አያስፈልግም። ከትልልቅ ማእከላዊ ባንኮች መውደቅ እስከ ትልቁ የአሜሪካ ዶላር መዳከም አለም በብዙ መልኩ የፋይናንስ ስርዓቷ ወደመፍረስ እየተጠጋ ለመሆኑ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ብቻ በቂ ማስረጃዎች ናቸው። እጅግ ከገዘፉ የሀይፐር ኢንሌሽን ክስተቶች እስከ አለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ኢ-እኩልነት በሚዘልቀው ይኸው የነባሩ የፋይናንስ ስርዓት ችግሮች በዘለለ የአለምን መዘውር በሚዘውሩት ታላላቅ ኢኮኖሚዎች ላይ ጥገኛ እስከመሆን እና ያለነሱ መንቀሳቀስ እስካለመቻል የሚዘልቀው ይኸው ችግር የሚያመላክተው የፊያት ገንዘቦቻችን በጠነከረ መሰረት ላይ የታነፁ ከጀርባቸውም ማስተማመኛ የሚሆን ምንም አይነት ጠንካራ ምሰሶ እንደሌላቸውም ማሳያ ነው። በአጭሩ አሁን ያለንበት የአለም የፋይናንስ ስርዓት የአለም ህዝብን ለመጥቀም የታነፀ ሳይሆን በአለም አቀፋዊ ገናና እና ጉልበተኛ አገረ መንግስቶች ጡንቻ እና ቁጥጥር ላይ የተመረኮዘ እና ያንንም ለማስፈፀም ተግባራዊ የሆነ ሁነት መሆኑን እያደርም ቢሆን ለአለም ግልፅ ሆኗል።
ታዲያ ይህንን የመቆጣጠሪያ ሰንሰለት ለመበጠስ እና ፋይናንሳዊ ነፃነትንም ለማወጅ ራሱን የቻለ ሌላ አማራጭ የግብይት ስርዓት አስፈላጊ ሊሆን ግድ ሆኗል። ቢትኮይን ይህን የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ የመጣ በምንም አይነት ማእከላዊ አስተዳዳሪ የማይመራ እና ማንም ሊጠቀመው የሚፈልግ ግለሰብ ባለቤቱ ሊሆን የሚችል የከረንሲ ስርዓት ነው። ምንም አይነት አገረ መንግስት ሊቆጣጠረው የማይችል በመሆኑም ህዝቦች እንደተመረጠው መንግስታቸው እሳቤ እና በሚያራምደው ፖሊሲ ብቻ ታጥረው መቀጠል ግድ እንዳይሆንባቸው አድርጓል። ቢትኮይን እና የብሎክቼይን ስርዓት እነዚሁ የአገረመንግስታትን መንበር የያዙ አካላትም ለጥቅማቸው ሲሉ እንደፈለጉት የሚታምቱ አልያም ከገበያ የሚያወጡት የገንዘብ ኖት ህትመት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጫ የሚያገኝበትን መንገድ ከፍተዋል።
ታዲያ ይህ ሁነት እስካሁን ስንፈልገው የነበረውን የፋይናንስ ነፃነት የሚያውጅ መፍትሄ ይሆን ይሆን?
በሂደት ይህንኑ ሁነት በቀጣይ የምንመለከት ይሆናል። በቀጣይ ክፍል በእርግጥም ቢትኮይንን የሚቆጣጠረው አካል ከሌለ እንዴትስ ሊዘወር አስቻለው የሚለውንና ከኢማእከላዊነቱ ጋር የተያያዙ እሳቤዎቹን የሚዳሰስ ይሆናል።
በሚስራ ሀሰን