ካንሰርን በማሽን ለርኒንግ
ባለብዙ ስልተ-ቀመር ማሽን ለርኒንግን ጥቅም ላይ በማዋል የካንሰር ታማሚዎች ለሕክምናው የሚያሳዩትን ምላሽ ለማወቅ የሚረዳ ሥርዓት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡
የማሽን ለርኒንግ ስልተ-ቀመሩ በሕክምና ሂደት ጥቅም ላይ ለሚውሉ ካንሰርን ለሚዋጉ መድኃኒቶች የታማሚዎችን ምላሽ ቀድሞ ለመተንበይ ያስችላል፡፡
በዚህም በሕክምናው ዘርፍ ያሉ መጠነ ሰፊ እና ውስብስብ ዳታዎችን በመሰል ሥርዓቶች በመተንተን የሕክምና ባለሞያዎች ለእያንዳንዱ ታማሚ ምን አይነት የሕክምና ሂደት መከተል እንደሚገባቸው የሚያስገነዝብ መረጃ እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡
ሥርዓቱን የጂዮርጂያ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና የኦቫሪያን ካንሰር ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች በጋራ በመሆን እንዳበለፀጉት ሄልዝ አይ.ቲ አናሊቲክስ አስነብቧል፡፡
የምርምር ቡድኑ ሥርዓቱን ለማበልፀግ ከአሜሪካው ብሔራዊ የካንሰር ኢንስቲትዩት ከተወሰዱ 499 ሕዋሶች የተገኘውን ዳታ በመጠቀም ለ15 የካንሰር አይነቶች የሚውል የማሽን ለርኒንግ የትንበያ ሥርዓት ማበልፀግ መቻላቸው ተመላክቷል፡፡
ሥርዓቱ በ23 የማሕፀን ካንሰር ታማሚዎች ላይ ተሞክሮ 90 በመቶ ስኬታማ ነው፡
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና ሽቅብ እርሻ
ከሚታረስ መሬት እጥረት እና ምርታማነት መቀነሰ ጋር ተያይዞ ዓለማችን የምግብ እጥረት ያሰጋታል፡፡ ስጋቱን ለመቀነስ ቴክኖሎጂ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) የሚተዳደር ሽቅብ እርሻን (Vertical Farming) አስተዋውቋል፡፡
ይህ አይነት የእርሻ ዘዴ ሕንጻዎች ውስጥ እና ጣራ ላይ እንዲሁም በሌሎች አመቺ አነስተኛ የቤት እና የውጭ ስፍራዎች ወደላይ በሚደረደሩ መሰደሪያዎች አማካኝነት ዕፅዋትን የማብቀያ መንገድ ነው፡፡
ይህ ዘዴ በሰው ልጅ ቁጥጥር ስር በሆነ ከባቢ ውስጥ እንደመከናወኑ የዕፅዋቱን የእድገት ሂደት ለመከታተል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በአጋዥነት ይጠቀማል፡፡
ለዕፅዋቱ ግብዓት የሆኑ እንደ አፈር እና ማዳበሪያ የመሳሰሉትን ለመመጠን፣ የሙቀት መጠንን ለመከታተል፣ ተባዮችን ለመቆጣጠር፣ ዕፅዋቱን እና ከባቢውን የተመለከተ ዳታን ለማጠናቀር ሰው ሰራሽ አስተውሎት ጥቅም ላይ እንደሚውል አናሊቲክስ ኢንሳይት ያትታል፡፡
ማሽን ለርኒንግን በመጠቀም የአፈሩን ምርታማነት እና የእርጥበት ይዘቱን ለመከታተል እንዲሁም ወቅቱን እና የዕፅዋቱን ሁኔታ ያገናዘበ የብርሀን ምጣኔ ሳይቋረጥ ለማቅረብ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ተመራጭ ሆኗል፡፡
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ የበሽታ ምርመራ
ሂስቶፓቶሎጂ ይሉታል የሕክምናው ዘርፍ ባለሞያዎች፡፡ የሕብረህዋስ (tissue) በሽታዎች ጥናት እና ምርመራ ነው፡፡
ዘርፉን ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በማጣመር ሕዋስ (ሴል) ለመቁጠር፣ ሕዋሳት ላይ የሚከሰቱ እንግዳ ክስተቶችን ለመለየት፣ በበሽታ የተጠቁ እና ጤነኛ ሕዋሶችን ለይቶ ለመመደብ እንዲሁም የሕዋሳት ምስሎች ላይ ያሉ ንድፎችን የመለየት አገልግሎት በቴክኖሎጂው እየታገዘ ነው፡፡
በዚህ ረገድ በሀገረ አሜሪካ ቦስተን ግዛት መቀመጫውን ባደረገ ፓዝኤ.አይ የተባለ የሕክምና ቴክኖሎጂ ተቋም አማካኝነት የበለፀገን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓት ለአብነት ማየት እንችላለን፡፡
የተቋሙ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤት የማሽን ለርኒንግ ስልተ-ቀመሮችን በመጠቀም ከታማሚዎች የተወሰደ ሕብረህዋስን (tissue) ልዩ ባሕርያት መሠረት አድርጎ ምርመራ እና ተገቢውን ሕክምና የመስጪያ መንገድ እንደሚያመላክት ቢይልት ኢን ድረ-ገጽ አስነብቧል፡፡
የፈጠራ ውጤቱ ለታማሚዎች የሚደረግ ምርመራን አግባብነት ከማረጋገጥ ባለፈ ታካሚዎች ለህመማቸው ትክክለኛውን ሕክምና እንዲያገኙ እያስቻለ ይገኛል፡፡
ይህን የረቀቀ በሽታዎችን የመመርመሪያ መንገድ በስፋት አበልፅጎ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ኩባንያው ከቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ የበጎ አድራጎት ተቋም ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡
ቴሌሄልዝ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ
ቴሌሄልዝ ጤና-ነክ የሆኑ አገልግሎቶች እና መረጃዎችን የቴሌኮም ቴክኖሎጂዎች እና መሣሪያዎችን በመጠቀም በርቀት ለሚገኝ የአገልግሎቱ ፈላጊ የማቅረብያ መንገድ ነው፡፡
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ በዓለም ዙሪያ አገልግሎቱ እየተስፋፋ የሚገኘው ይህ የሕክምና መንገድ ለአገልግሎቱ ጥራት እና ለተደራሽነቱ ስፋት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ጥቅም ላይ እያዋለ ይገኛል፡፡
ኢመርጅ የተባለው ድረ-ገጽ ዘርፉን አስመልክቶ በሰራው ሀተታ ከታማሚዎች የሕክምና መዝገብ የሚሰበሰብ መረጃን በማሽን ለርኒንግ በመተንተን ለሐኪሞች ውሳኔ የሚያገለግል ተጨማሪ ዕይታን ያበረክታል፡፡
በሌላ በኩል በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚታገዙ መሣሪያዎች በርቀት የሚገኙ ታማሚዎች እና ክትትል የሚያሻቸው አረጋውያንን የልብ ምት፣ የሙቀት መጠን እና የደም ግፊት የመሳሰሉ አስፈላጊ ምልክቶችን በመከታተል ችግሮች ሲኖሩ ለጤና ባለሙያዎች ያሳውቃሉ፡፡
ከዚህም ዘለል ሲል በርቀት መቆጣጠሪያ አማካኝነት በሮቦት አጋዥነት የሚከናወኑ ቀዶ ህክምና ድረስ አስተዋጽዎ እያበረከተ ነው፡፡
በዚህ ዘርፍ ሌላኛው አገልግሎት በማሽን ለርኒንግ የበለጸጉ ቻት ቦቶች (የውይይት መለዋወጫ ሮቦቶች) የሚሰጡት ነው፡፡ ቻትቦቶቹ ታማሚው የሚሰጣቸውን የበሽታ ምልክቶች እና ሌሎች መረጃዎች መሠረት አድርገው የምርመራ ድጋፍ ማድረግ ችለዋል፡፡
ተመሳሳዩ የህክምና አገልግሎት በኢትዮጵያም እውን እንዲሆን ኢንስቲትዩታችን አመርቂ ጥረት ላይ ሲሆን ለጤናው ዘርፍ አበርክቶው ከፍ ያለ ይሆናል፡፡
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በትምህርት ዘርፍ
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በጎ ተፅዕኖውን ካሳረፈባቸው ዘርፎች መካከል ትምህርት አንዱ ነው፡፡
ከቴክኖሎጂው አበርክቶዎች መካከል፡-
• ለተማሪው እንዳቅሙ የተመጠነ የትምህርት አሰጣጥ ለመቅረጽ፣
• አጋዥ ትምህርቶችን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቻትቦቶች አማካኝነት ለማቅረብ፣
• ምናባዊ የትምህርት ከባቢን ለመፍጠር፣
• የተለያዩ ምዘና እና ፈተናዎችን ከማጭበርበር ሂደቶች እንዲሁም ከደህንነት ስጋቶች ለመጠበቅ ይጠቀሳሉ፡፡
ለትምህርት ሂደቱ መሻሻል በቴክኖሎጂው አማካኝነት በተግባር ከዋሉ መጠቀሚያዎች መካከል ዳታሜሽን ድረ-ገጽን ዋቢ አድርገን ሁለቱን እንመልከት፡፡
Gradescope፡- ይህ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያ መምህራን የተማሪዎቻቸውን ደረጃ በቀላሉ እንዲረዱ የሚያስችል ነው፡፡ ተማሪዎች የሚሰጣቸውን የቤት ሥራ በመተግበሪያው ላይ በመጫን ውጤታቸውን ለተገቢው አካል ያሳውቃል፡፡
በተጨማሪም የእያንዳንዱን ተማሪ የብቃት ደረጃ ተንትኖ በማሳወቅ መምህራን ተጨማሪ እገዛ እና ምክር የሚያስፈለጋቸውን ተማሪዎች በቀላሉ ለመለየት ያስችላቸዋል፡፡
Content Technologies, Inc. (CTI) ፡- ዲፕ ለርኒንግን በመጠቀም ተማሪውን ባማከለ ሁኔታ የትምህርት ይዘቶችን በማዘጋጀት ላይ የሚያተኩር ሶፍትዌር አምራች ኩባንያ ነው፡፡
የኩባንያው ሶፍትዌር የትምህርት ግብዓቶችን በመተንተን የተመጠኑ ይዘቶችን ተማሪዎችን ለምዘና የሚያዘጋጁ የምርጫ ጥያቄዎችን ያዘጋጃል፡፡