የጃፓኑ መኪና አምራች ቶዮታ ኩባንያ የሰዎችን በጨረቃ ላይ የመኖር እቅድ ሊያሳካ ይችላል የተባለለት መኪና ሊያመርት መሆኑን አስታወቀ፡፡
ከጃፓኑ የሕዋ ተቋም ጋር በጥምረት ወደ ስራ የገባው ቶዮታ ኩባንያ መኪናውን በአውሮፓውያኑ 2020ዎቹ መጨረሻ ወደ ጨረቃ የመላክ እቅድ እንዳለው ዴይሊ ሜይል አስነብቧል፡፡
ሉናር ክሩዘር የሚል መጠሪያ የተሰጠው መኪና ሁለት ሰዎችን የመያዝ አቅም ሲኖረው በጨረቃ ላይ ለአስራ አራት ቀናት ያህል ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ለመስራት እና በውስጡ ለመኖር ያስችላል፡፡
ተሽከርካሪው በሚኖረው የሮቦት እጅ አማካኝነት የተለያዩ ምርመራዎችን እና ጥገናዎችን ማከናውን እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ የሮቦት እጁ ከባድ ነገሮችን ለማንሳት እና የተለያዩ መሣሪያዎችን ለመያዝ እንዲያገለግል ጫፉን መቀያየር የሚቻል መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የሰው ልጅ በጨረቃ እና በሌሎችም የሕዋ አካላት ላይ ለሚያደርገው የጥናት እና ምርምር እንዲሁም በቀጣይ ለመኖሪያ አማራጭ ፍለጋው መኪናው እገዛ እንደሚያደረግ ይጠበቃል፡፡