በአሁኑ ወቅት የሳይበር ጥቃት በአይነትም፣ በመጠንም በዝቶ ተጠቃሚዎችን በከፍተኛ ስጋት ላይ በመጣል ላይ ይገኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም እየተለመዱ ከመጡ የጥቃት አይነቶች መካከል ኢንፎርሜሽንን ማገት ወይም ራንሰምዌር የሚባለው ጥቃት ይጠቀሳል፡፡ ራንሰምዌሮች ባእድ የሆኑ አጥፊ ሶፍትዌሮች ሲሆኑ ሶፍትዌሮቹ ዲዛይን ሲደረጉ የኮምፒውተር ሲስተሞችን በመዝጋት ለተዘጋው ሲስተም ክፍያ እንዲፈጽሙ በማሰብ የተዘጋጁ አጥፊ ሶፍትዌሮች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የእነዚህ ራንሰምዌሮች ጥቃት እየረቀቀና እየሰፋ ብዙ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ኪሳራና ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡
የራንሰምዌር ጥቃት ከማልዌር ቤተሰብ የሚመደብ ሲሆን ጠቃሚ ሶፍትዌር ወይም ፋይል እንዲሁም አፋጣኝ ምላሽ የሚፈልግ ማስጠንቀቂያ (Popup notification) በመምሰል ኮምፒዩተራችን ላይ ከጫንነው በኋላ የተወሰኑ ወሳኝ ፋይሎችን ወይም ኮምፒዩተሩን በአጠቃላይ በመመስጠር ወይም (Encrypt በማድረግ) ፋሎቹን መክፈት እንዳንችልና ተደራሽ እንዳይሆኑ የማድረግ ተግባር ይፈፅማል፡፡ ይህንን ጥቃት ለየት የሚያደርገው ፋይሎቹን ወይም ኮምፒዩተሩን ተጠቃሚዎች መጠቀም ከፈለጉ በቢትኮይን እና በሌሎች የኦንላይን የመክፈያ ስርአቶች በመጠቀም እንዲከፍሉ የሚያስገድድ መሆኑ ነው፡፡ ይሁንና ተጠቃሚዎች ልብ ሊሉት የሚገባው ጉዳይ ገንዘቡ ከተከፈለም በኋላ ኮምፒውተሩ ወይም ሲስተሙ መለቀቁ ዋስትና አለመኖሩ ይህን የቫይረስ ጥቃት ለየት ያለ ያደርገዋል፡፡
ኮምፒውተር በተለያዩ ምክንያቶች በዚህ የራንሰምዌር ማልዌር ጥቃት ሊጋለጥ የሚችል ሲሆን ከነዚህም መካከል በኦፕሬቲንግ ሲስተም ዲዛይን ላይ በሚፈጠር ችግር፣ በአንድ ኔትወርክ ውስጥ ሁሉም ኮምፒውተሮች ተመሳሳይ ኦፕሬቲንግ ሲስተም የሚጠቀሙ ከሆነ ወይም ለተጠቃሚዎች በርካታ ፈቃዶችን የሚሰጥ ከሆነ በቀላሉ ለጥቃት ሊጋለጥ ይችላል፡፡ ራንሰምዌር ከአጥፊ ሶፍትዌሮች መካከል አንዱ እና በአለማችን ትልቁ የሳይበር ምህዳር ስጋት እንደመሆኑ መጠን በየጊዜው በሰዎች ላይ እያደረሰ ያለው ሁለንተናዊ ጉዳት በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም፡፡
በፈረንጆቹ 2019 ብቻ በራንሰምዌር አማካኝነት በተፈጸም የሳይበር ጥቃት 11.5 ቢሊዮን ዶላር ዓለም አቀፍ ኪሳራ ተመዝግቦ እንደነበር መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን ይህ የሳይበር ስጋት ባለፉት ሁለት ዓመታትም ይበልጥ አየጨመረ ይገኛል፡፡
እነዚህ የሳይበር ጥቃቶች የተጠቃሚውን መረጃ በመቆለፍ የመረጃው ባለቤት ያከማቸውን ዳታ መመልከት እንዳይችል በማድረግ የሚፈጸም የሳይበር ወንጀል በመሆኑ ብዙዎች ወሳኝ የሚሉትን መረጃ መልሰው ለማግኘት ለጥቃት አድራሹ ክፍያ ለመፈፀም ሊጋፋፉ ይችላሉ፡፡ ይሁንና ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው አንዴ ገንዘብ ተከፍሎ መረጃው ለባለቤቱ በአስተማማኝ ሁኔታ ይመለሳል የሚለው እና ከዚህ በኋላም ለጥቃት የመጋለጥ እድሉ ጥያቄ የሚነሳበት በመሆኑ ለጥቃት አድራሾች ምንም አይነት ገንዘብ አለመክፈል በብዙዎች የሚመከረው ጉዳይ ነው፡፡
በዚህ የሳበር ጥቃት ዙሪያ የተሰሩ የቅርብ ጥናቶች እንደሚሳዩት የራንሰምዌር ቫይረስ የማኒዩፋክቸሪን ዝርፉን በዋናነት ኢላማ እያደረገ መምጣቱ የሚነገር ሲሆን ከዛ በተጨማሪም የፋይናንስ ዘርፉ፣ ትራንስፖርት፣ የጤና ተቀዋማት እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች በተከታይነት ተቀምጠዋል፡፡ ሳይበር ክራይም የተባለ አለም አቀፍ ጋዜጥ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው የራንሰምዌር ጥቃት በአለማችን ዙሪያ በየአስራ አንድ ሰኮንዱ በአንድ ግለሰብ ወይም ተቋም ላይ የሚደርስ ሲሆን እስከ 2021 አጋማሽ ብቻ 1,097 በሚሆኑ አነስተኛና ትላልቅ ተቋማት ሊደርስ ችሏል፡፡
ይህ የሳይበር ስጋት በየትኛውም ሁኔታና አጋጣሚ የግል ኮምፒውተራችንን አልያም የተቋም ሰርቨርና የኔትወርክ ደህንነትን አደጋ ውስት ሊከት በመቻሉ ሁልግዜም ወሳኝ የምንላቸውን የመረጃ ግልባጭ ወይም (Back up) መያዝና ማስቀመጥ እጅግ የሚመከር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ አደገኛ ሶፍትዌሮች በግል ኮምፒውተራችንን እና በተቋሞቻችን ሃብት ላይ ጥቃት ከማድረሳቸው በፊት ልንወስዳቸው የሚገቡ መሰረታዊ ጥንቃቄዎች መካከል ሁሉንም አይነት ሶፍትዌሮች፣ አፕሊኬሽኖችንና ኦፕሬቲንግ ሲስተሞችን በየወቅቱ ማሻሻል፤ የታደሱ ፀረቫይረሶችን በመጠቀም በየጊዜው ኮምፒዩተራችንን ስካን ማድረግ፤ ተጋላጭነታችን ሊያሰፉ ከሚችሉ አጠራጣሪ ድረ-ገፅች፣ መተግበሪዎችና ፋይሎች ረሳችንን መጠበቅ፤ የማናውቃቸውን ኢሜይሎች አለመክፈትና የተላኩ አባሪዎችንም ዳውንሎድ አለማድረግ፤ በየጊዜው የሚመጡ ማስታወቂያዎችን ምላሽ ከመስጠታችን በፊት በጥንቃቄ መመልከት እና የራንሰምዌር ጥቃት እየደረሰ መሆኑ ከታወቀ ባለሙያ በማማከር ማልዌሩን በአፋጣኝ ማጥፋትና ቫይረሱ ወደሌሎች እንዳይሰደራጭ ጥቃት የደረሰበትን ኮምፒውተር ለይቶ ማስቀመጥ እጅግ ይመከራል፡፡