ኢትዮ ቴሌኮም የሦስት ዓመት አዲስ የእድገት ስትራቴጂውን በ2015 በጀት ዓመት መጀመሪያ ካስተዋወቀ በኋላ የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ሪፖርቱን በዛሬው እለት አቅርቧል።የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ እንደተናገሩት ኩባንያው ባለፉት ስድስት ወራት 8.18 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት የኩባንያው የዓመቱ ሙሉ ገቢ 9 ቢሊየን ብር የነበረ ሲሆን በ2015 ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ የተገኘው ገቢ ካለፈው ሙሉ ዓመት ገቢ ጋር የሚስተካል መሆኑ ተገልጿል።በዘንድሮው ዓመት ለተገኘው ከፍተኛ ትርፍ ዋና ምክንያት የሚሆነው በኩባንያው የተደረገው የወጪ ቅነሳ መርሃ ግብር እና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መተግበሩ 3.5 ቢሊዮን ብር ወጪ መቀነስ እንዳስቻለ ፍሬህይወት ታምሩ መናገራቸውን ብስራት ሬዲዮ ሰምቷል።
ኢትዮ ቴሌኮም 214 ከሚሆኑ ተቋማት ጋር በቴሌ ብር አጋርነት እየሰሩ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት 217 ቢሊየን ብር በቴሌ ብር መዘዋወሩ ተጠቁሟል ።ኢትዮ ቴሌኮም አጠቃቀምን ለማሳደግ የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያ ፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም የደንበኞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ 50 አዳዲስ እና 41 ነባር በድምሩ 91 የሀገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎት ማሻሻሉን ገልጿል ።
የቴሌብር አገልግሎት ከ27.2 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ማፍራት የቻለ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ውስጥ የ168.1 ቢሊዮን ብር የግብይት መጠን በማንቀሳቀስ በቴሌ ብር 82.5 ሚሊዮን ብር ገቢ ማስገኘት ተችሏል።